ከዚህ ቀደም፣ ‹ዛጎል›፣ ‹ደርሶ መልስ›፣ ‹እምቢታ (የቃቄ ወርድወት)› እና ‹ምሳሌ› በተሰኙ ረጃጅም ልቦለዶቹ የምታውቁት፤ በጭብጥ አመራረጡና በአጻጻፍ ስልቱ የተወዳጃችሁት እንዳለጌታ ከበደ፣ አሁን ደግሞ ‹ሲጥል› የተሰኘ ልቦለድ አበርክቶልናል፡፡
‹ሲጥል› የመንገደኞች ታሪክ ነው፤ መንገደኞቹ ለየጉዳዮቻቸው ከቤታቸው ወጥተው አንድ ላይ ቢሳፈሩም፣ በአንድ ባልታሰበ ሰበብ አብረው የሚሰነብቱበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡ መንገደኞቹ፣ የየራሳቸው የሕይወት ፍልስፍና እና መርሆ ያላቸው ናቸው፡፡ እናም፣ በረገጡት ሥፍራ እንግዳ የሚሆኑት እነሱ ብቻ አይሆኑም - ሃሳቦቻቸውም ጭምር እንጂ፡፡
‹ሲጥል› እንደ ከዚህ ቀደም የእንዳለጌታ መጻሕፍት ከራሳችን ጋር የሚያጨዋውቱ፣ ለሙግትም የሚጋብዙ ሃሳቦች የተስተናገዱበት ኪናዊ ማዕድ ነው፡፡ የድኅረ ዘመናዊ ደራስያንን የአጻጻፍ መንገድ በከፊል ተከትሎ፣ የትረካ ስልቱን ደግሞ እንደ ጃዝ ሙዚቃ አድርጎታል፡፡ በጃዝ ሙዚቃ እያንዳንዱ ተሳታፊ ሙዚቀኛ በተናጠል ስሜቱንና ሃሳቡን ለዕድምተኛው የሚያጋባበት፣ ችሎታውን የሚያስፈትሽበት ጥቂት ‹ዕድል› እንዳለው ሁሉ፣ የ‹ሲጥል› ገጸባህርያትም አንዳንዴ ለየብቻ - ከዐውዱ ሳይነጠሉ፣ ድባቡንም ሳያውኩ - ኑረታቸውን ይተርኩልናል፤ እነዚህ ለየብቻ ሲጫወቱልን የቆዩ ተራኪዎች ተመልሰው ደግሞ በኅብር ይከይኑልናል… ፍቅርና ጥላቻን…ሣቅና ሲቃን…ፍርሃትና ድፍረትን… ‹መሆን ወይም አለመሆን›ን! |